የአማራ ማህበር በቤኤርያ (አማቤ)
መተዳደሪያ ደንብ / ፳፻፲፭
መግቢያ
የአማራ ህዝብ መዋቅራዊ በሆነ ግፍ እና አይን ያወጣ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሀገራችን በኢትዮጵያ እየተፈጸመበት ይገኛል። በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው የአምሓራ ህዝብ የምግብ ዋስትና የሌለው፤ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የሚሰቃይ ፤ የመሠረታዊ ትምህርት ተደራሽነት የሌለው ሲሆን፤ ለከፍተኛ ድህነት ፤ ለጦርነት እና ለእርስ በርስ ግጭት ፤ በሀገር ውስጥ መፈናቀል እና ለውጭ ሀገር ስደት ተዳርጓል። እንዲሁም የመምረጥ እና የመመረጥ መብቶቹን በመግፈፍ፤ ሆን ተብሎ ከስልጣን እንዲገለል በማድረግ፤ ፍትሃዊ የሃብትና የንብረት ባለቤት እንዳይሆን በተደራጀና በተጠና መዋቅር ሲሰራበት ቆይቷል። ባጠቃላይ የአማራ ሀዝብ በተደጋጋሚ ጦርነት ኢኮኖሚው እንዲወድም ተደርጎበታል። ይህ የአምባ ገነን ሥርዐት በአማራ ወገኖቻችን ላይ የከፈተውን የህልውና ጦርነት ለአለም መንግስታት በማሳወቅ እና የአማራን ህዝብ ለነጻነት፣ለእኩልነት፣ ለለፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና አካታች ሐገራዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ፤ በጉልበትና በሀይል የተወሰዱ የአማራውን እርስት ለማስመለስ በሚደረገው የሰላማዊ ትግል መሳተፍና ማገዝ ወቅታዊ እና ቸል ሊባል የማይገባው መሆኑን ተረድተናል።
በመሆኑም የአማራ ህዝብ ነጻነት በገጠመው የህልውና ፈተና ላይ የራሳችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት፤ መላው የአማራ ተወላጅ የሆነ ሁሉ ከጎጥ ከፆታና ከሀይማኖት ልዩነት ሳይገድበው የአማራ ህዝብ በኢትዩጵያ ማህበራዊ፣ እኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለዘለቄታ መፍትሄ ለማምጣት እንዲያግዝና ከድህነት ለማላቀቅ በሚደረግ ጥረት ሁሉ እንዲተባበር በማመን፤ የሚመሰረተው የቤይ ኤርያ የአማራ ማህበር አሁን ኢትዮጵያን ከሚገዛው የብልፅግና ፓርቲ እንዲሁም ከአማራ ብልፅግና ፓርቲ ተጽዕኖ የፀዳ፤ በሚታመኑ እውነተኛ የአማራ ተዋላጆች በሚመርጠው አመራር በሚያስቀምጠው ግብና በሚነድፈው ዕቅድ እንዲንቀሳቀስ አና እንዲመራ ፤ የቤይ ኤርያ የአማራ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግለት በማመን፣ የቤይ ኤርያ የአማራ ማህበር ሰኔ ፲, ፳፻፲፭ ዓ.ም. (June 17, 2023) በኦክላድ ከተማ፤ በካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት ተቋቋመ።
አንቀጽ 1፡ የማህበሩ ስያሜ
የማህበሩ ስም/ስያሜ ከዚህ በኋላ "የአማራ ማህበር በቤይ ኤርያ" ወይም "አማቤ" ወይም Amhara Association of Bay Area ወይም (AABA) ተብሎ ይጠራል።
አንቀጽ 2፡ የማህበሩ አርማ
የአማራ ማህበር በቤይ ኤርያ የድርጅት አርማ ንስር አሞራ ነው። ንስር አሞራ ፀሐይን ቀጥ ብሎ ማየት የሚችል ወደ ጸሐይ አቅጣጫ ጨረሩን እያየ መብረር የሚችል ብቸኛው የአለማችን ፍጥረት ነው ። በተጨማሪም ንስር አሞራ ከሰው አይን 8 እጥፍ የተሻለ ማየት ይችላል። በተጨማሪም ንስር አሞራ ከ360° በአንድ እይታ ማየት የሚችል ድንቅ ፍጥረት ነው። በዚህ ምክንያት ንስር አሞራን የአማራን ህዝብ አርቆ አሳቢነት ስለሚያመለክት፤ የድርጅቱ አርማ ሆኖ ተመርጧል። የአማራ ህዝብ በእውነትም አርቆ አሳቢ ነው፤ ለዘመናት ያጎለበተው የጀግንነት፤ የፍትሀዊ ፤ ሁሉንም በእኩል የማየት እሴቱን እና የአስተሳስብ ብቃቱን ያሳያል።
አንቀጽ 3፡ አድራሻ
Amhara Association of Bay Area
1319 Washington Avenue Unit 551
San Leandro, CA 94577
Zelle donation: amharabayarea@gmail.com
አንቀጽ 4፡ የደንቡ ተፈጻሚነት
ይህ የአማራ ማህበር ቤይ ኤርያ መተዳደሪያ ደንብ በሰሜን አሜሪካ፣ በካሊፎርንያ ቤይ ኤርያ በሚኖሩ የማሀበሩ አባላት ላይ ተፋጻሚ ይሆናል:: "የአማራ ማህበር በቤይ ኤርያ" ማለት በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ኦክላንድ ፤ ካሊፎርኒያ ሰኔ ፲, ፳፻፲፭ ዓ.ም. (June 17, 2023) ዓ/ም የተቋቋመው ቦርድ - መር ድርጅት ነው።
አንቀጽ 5 ፡ ምዝገባ
ማህበሩ በአሜሪካ የማህበራት ማቋቋሚያ ህግ 501(C)(3) መሰረት ለትርፍ ያልተቋቋመ ሆኖ ተመዝግቧል።
“የአማራ ማህበር በቤይ ኤርያ አካውንት” ማለት በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ፤ በቤይ ኤርያ ውስጥ በማንኛውም ባንክ የሚከፍተው የባንክ አካውንት ማለት ነው።
“የአማራ ዳያስፖራ” ማለት ከኢትዮጵያ ውጪ በቋሚነት የሚኖር የኢትዮጵያ ዜግነት ያለው አማራ የሆነ ወይም የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነ የውጭ ዜግነት ያለው አማራ ማለት ነው።
“ቦርድ” ማለትት ማህበሩ ሲመሰረት ይዞ የተነሳውን ዓላማ ለማስፈጸምና የበላይ ሆኖ ይህ ማህበር ግቡን እንዲመታ የሚያደርግ የበላይ ጠባቂ ማለት ነው።
የአማራ ማህበር በቤይ ኤርያ የገቢ ምንጭ ማለት ፤ ከአማራ ዲያስፓራ እና የአማራ ወዳጅ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ የሚገኘውን መዋጮ ማእከል አድርጎ ፣ በቦርድ ውሳኔ መሠረት ከሕዝባዊ መዋጮ ፣ ከገቢ ማስገኛ ስራዎች ፣ ከእርዳታ ሰጪዎች ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ፣ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ የኢትዮጵያ እና የአማራ ወዳጆች ፤ የግል ድርጅቶች እና ማህበሩን ለመርዳት ፍላጎት ካላቸው ኢትዮጵያውያን የሚገኝ ገንዘብ ወይም ንብረት ማለት ነው።
አንቀጽ 6፡ የማህበሩ ራዕይ
የአማራ ህዝብ የማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ የህልውና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተማማኝ ድርጅት ሆኖ ማየት።
አንቀጽ 7፡ የማህበሩ ተልዕኮ
1. በቤይ ኤርያ የሚኖሩትን የዐማራ ማኅበረሰብ ኅብረት እና አንድነት ማጠናከር፤
2. የዐማራን ሕዝብ ባህል በቤይ ኤርያ አካባቢ ማጎልበት እና ማስተዋወቅ፤
3. በቤይ ኤርያ አካባቢ የሚኖረውን የዐማራ ማኅበረሰብ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በሥራ መስክ እና በትምህርት ዘርፍ እርስ በእርስ የሚረዳዳበትን መርኃ ግብሮች መዘርጋት፤
4. የቤይ ኤርያ የዐማራ ማኅበረሰብ በአካባቢው ባለው የዐማራ ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው እንዲሆን እና ተሰሚነት እንዲያገኝ ተፅዕኖ መፍጠር ናቸው።
አንቀጽ 8፡ የማህበሩ አላማ
በካሊፎርኒያ ግዛት በቤይ ኤርያ አካባቢ ጠንካራ እና የተደራጀ የአማራ ማህበር መመስረት
የአማራ ህዝብ ላይ የሚታየውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ፕሮግራም በመንደፍ መስራት።
በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመጠቀም በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ለኢንተርናሽናል ኮሚኒት ማሳወቅ።
በውጪ ሃገር ከሚኖሩ የአማራ ማህበረሰብ እና በመላው አለም ከሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ግለሰቦች ገንዘብና እውቀት በማሰባሰብ የአማራ ማህብረሰብን ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት።
የምንሰራቸው ፕሮጀክቶች ፤ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ የውሃ እና የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና መጠበቂያ ተቋማት ፣ የአዛውንቶች እና የአካል ጉዳት ማገገሚያ ፣ የግብርና ልማት፣ ቴክኖሎጂ፣ አነስተኛ ሥራ ፈጣሪነት እና ሌሎች የገቢ እና የስራ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኩራል። በወጣቶች ፣ በሴቶች ፣ ገበሬዎች ላይ ትኩረት ለሚሰጡ ፕሮጀክቶች ፤ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ይሆናል።
ለአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም እና መብት መከበር በሰላማዊ መንገድ ተግተው የሚንቀሳቀሱ አካላትን መደገፍ እና ማጠናከር።
በውጪ ከሚኖረው የአማራ ማህበረሰብና በሃገር ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ሁሉንም አካታችና ፍትሓዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና እንዲፈጠር እገዛ ማድረግ።
የአማራ ህዝብ ፍትሃዊ የልማት እኩል ተጠቃሚነት ፣ የፍትህ፣ የወሰን እና የርስት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን በገንዘብ በእውቀት እና በቁሳቁስ መደገፍ።
አንቀጽ 9፡ የቤኤርያ መደበኛ አባላት
የአማራ ማህበር በቤኤርያ ፤ የአማራን ማህበራዊና አኤኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍና ለችግር የተጋለጠውን ወገናችንን ኑሮ በዘላቂነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ፕሮጄክቶችን ፤ የቤኤርያ አማራ አባል በመሆን በቋሚነት በገንዘብም ሆነ በእውቀት እንዲረዱ ያንቀሳቅሳል፣ ያበረታታል። ድጋፋቸውንም ለማበረታታት በመደበኛ እና በክብር አባልነት ይመዘግባል።
መደበኛ አባላት ማለት በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቀርቦ በማህበሩ ቦርድ ውሣኔ ተቀባይነት ያገኙ አባላት ማለት ነው።
የሚከተሉትን መመዘኛዎች የሚያሟላ በውጪ የሚኖር የአማራ ተወላጅ ፤ መደበኛ አባል መሆን ይችላል፤
2.1. አማራ የሆነ እና በአማራነት መደራጀትን የተቀበለ፤
2.2 የማህበሩን አላማ፣ ግብ፣ፖሊሲና የሚያስቀምጣቸውን ግዴታዎች የሚቀበል፤
2.3 እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ፣ የድርጅቱ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በቦርዱ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየጊዜው የሚወጡ የሥነ-ምግባር ደንቦችን የሚቀበልና ተግባራዊ የሚያደርግ፣
2.4 በቦርድ አባላት ( በጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነውን ወርሀዊ ክፍያና መዋጮ የሚከፍል)። በየጊዜው ስምምነት የሚደረግባቸውን ክፍያዎችና መዋጮዎች መክፈል የሚችል፤
2.5 በህግ መብቱ ያልተገፈፈ፡፡
አንቀጽ 10፡ የክብር አባላት
የድርጅቱ አባል ያልሆኑና የአማራ ማህበር በቤኤርያ አላማ ለማስፈጸም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ፤ ድርጅቱ በሚሰራባቸው ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማና የለውጥ አርአያ በመሆን በድርጅቱ አባላት ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ ግለሰቦች በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተገምግመው በማሕበሩ ቦርድ አባላት ውሳኔ የክብር አባል ይሆናሉ።
የክብር አባላት በድርጅቱ ውስጥ የመምረጥ ፤ የመመረጥና ድምፅ የመስጠት መብት አይኖራቸውም፡፡
የክብር አባላት በራስ ተነሳሽነት ካልሆነ በቀር የአባልነት መዋጮዎችንና ሌሎች ክፍያዎችን የመክፈል ግዴታ አይኖርባቸውም።
አንቀጽ 11፡ የአባልነት መብት
ሁሉም መደበኛ አባላት እኩል መብት አላቸው።
ማንኛውም የማህበሩ መደበኛ አባል፡-
ለማህበሩ ዓላማና ተልእኮዎች መሳካት የሚጠቅሙ ማናቸውንም አይነት ስራዎች የመስራት፣
የማህበሩን እንቅስቃሴ በተመለከተ ማንኛውንም መረጃ በመደበኛ የሥራ ሰዓት ጠይቆ የማግኘት፣
በማህበሩ ስብሰባ የመገኘትና ስለድርጅቱ እንቅስቃሴ አስተያየትና ድምጽ የመስጠት መብት አለው።
አንቀጽ 12፡ የአባልነት ግዴታ
ማንኛውም አባል የአባልነት መዋጮን በወቅቱ የመክፈል፣
ማንኛውም አባል የማህበሩን የመተዳደሪያ ደንብ፣ በቦርድ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚወጡ መመሪያዎችና ውሣኔዎችን የማክበር፣
ማንኛውም አባል የማህበሩን አላማና የገባቸውን ግዴታዎች የማክበር፣ የማህበሩን ንብረት የመንከባከብና የመጠበቅ፣
ማህበሩ ዓላማውን ለማሳካት በሚጠራቸው ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ግዴታ አለበት።
አንቀጽ 13፡ የአባላት መዋጮና ሌሎች ክፍያዎች
የማህበሩ መዋጮና ሌሎች ክፍያዎች የሚደረጉበትን ጊዜና መጠን በጠቅላላ ጉባኤ አባላት ይወሰናል።
አንቀጽ 14፡ ከማህበሩ አባልነት ስለመሰናበት
ሲሞት፣
መተዳደሪያ ደንቡ ላይ በተገለጸው መሠረት ወይም በሌላ አጥጋቢ ምክንያት ከአባልነት እንዲሰናበት በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቀርቦ ቦርዱ ሲወስን፣
የማህበሩን ክብርና ህልውና በሚነካ ወይም በሚያናጋ ተግባር ላይ መሳተፉ በማስረጃ ሲረጋገጥና ይህም በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቀርቦ ቦርዱ በ ¾ ድምጽ ሲወሰን፣
ለማህበሩ ዓላማ መሣካት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተገቢውን ተሣትፎ ለማድረግ ፍቃደኛ ሳይሆን እና ይኸውም በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቀርቦ በቦርድ ሲወሰን፣
መዋጮውን ለተከታታይ 5- 6 ወራት ሳይከፈል ሲቀር፣
ከማህበሩ አባልነት በራሱ ፈቃድ ለመልቀቅ ሲወስን ይሆናል፣
አንቀጽ 15፡ የአማራ ማህበር በቤኤርያ አደረጃጀት
የአማራ ማህበር በቤኤርያ አስተዳደር ሦስት ዋና ዋና አካላት ይኖሩታል።
ጠቅላላ ጉባኤ ፤ የቦርድ አባላት እና የስራ አስጊያጅ ኮሚቴ ናቸው።
አንቀጽ 16፡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት
የአማራ ማህበር በቤኤርያ አባል የሆነ ሁሉ ስራውን በሙያዊ ብቃት፣ በታማኝነት እና በከፍተኛ የስነ ምግባር ደረጃ ማከናወን አለበት።
አንድ (የአማቤ) አባል ፤ የአማራ ህዝብ አሁን ባለው እና ቀድመው በነበሩት አገዛዞች ሆን ተብሎ በሚደርሱ ችግሮች እየተገደለ ፣ እየተሰደደ ፣ እርስቱ እየተወሰደ ፣ እምነት እና ባህሉን እንዳያከብር እየተደረገ ፣ የእምነት ቦታዎቹ እየወደሙ እንዳለ የተረዳ ፣ ወደስልጣን እንዳይመጣ እየተደረገ ፣ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየደረሰበት እንደሆነ የተረዳ መሆን አለበት። በተጨማሪም አባሉ የአማራ ማህበር በቤኤርያን መተዳደሪያ ደንብ እንዳነበበ እና እሱ ወይም እሷ በመተዳደሪያው እንደሚመሩ ወይም እንደሚታዘዙ ማረጋገጥ አለባቸው።
የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ አንብቤና ተረድቼው ስላመንኩበት ይህን የመተዳደሪያ ደንብ እቀበላለሁ።
ሙሉ ስም፡ ________________________________________ ፊርማ፡ _________________________ ቀን፡_____________________
Full Name: _______________________________________ Signature: _______________________ Date: _____________________
አንቀጽ 17፡ የጠቅላላ ጉባኤው ስልጣንና እና ተግባር
ጠቅላላ ጉባኤ የበላይ አካል ሲሆን አጠቃላይ አመራር ይሰጣል፣ ስትራቴጂና መመሪያ ያወጣል፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ያደርጋል፣
የቦርድ አባላት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል ጥያቄ ሲያነሱ፤ ጠቅላላ ጉባኤው ጥያቄውን ተቀብሎ ተወያይቶ፤ የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ በድምፅ ብልጫ ያሻሽላል።
አመለካከቱን በመወከል፣ መተዳደሪያ ደንቦቹን በመተርጎም እና ተልዕኮውን፣ ራዕዩን እና ግቡን በማስደገፍ ለድርጅቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ያድርጉ።
የማህበሩን የዕለት ተዕለት አስተዳደር እና ኃላፊነት የሚወከሉላቸውን የዳይሬክተሮች ቦርድ እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን መርጠው ይሰይማሉ።
የዳይሬክተሮች ቦርድ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የስራ ገለፃቸውን መሰረት በማድረግ አፈፃፀማቸውን ይገመግማሉ።
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን እና የዳይሬክተሮች ቦርድን የአመራር አቅምን፤ ጥራቶችን፤ የቴክኒካዊ እውቀትን በእቅድ እና አፈፃፀም ላይ እና የድርጅቱን እና የጥቅሞቹን አጠቃላይ አስተዳደር ይቆጣጠራል።
አንቀጽ 18፡ የቦርድ ስልጣንና ተግባር
በዚህ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በጠቅላላ አባል ጉባኤ በተሰጠው ስልጣን ማንኛውንም የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ተግባር እና ስልጣን ለመሾም ለመሻር ተፈቅዶለታል። ቦርዱ በዚህ መተዳደሪያ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ይሆናል። የማህበሩ የዳይሬክተሮች የቦርድ ፕሬዝደንት ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ ፀሀፊ ፣ የህዝብ ግንኙነት እና የውስጥ ኦዲተር በአጠቃላይ አባልነት የሚመረጡ እና የሚያገለግሉ ናቸው። እያንዳንዱ የቦርድ ኦፊሰር ስልጣን ይኖረዋል እና ከዚህ በታች የተቀመጡትን ተግባራት ያከናውናል::
ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለሚቀረቡ ፕሮጄክቶች እና ተቀባይነት ላገኙ አጋር ድርጅቶች ገንዘብ እንዲለቀቅላቸው የስራ አስካያጅ ኮሚቴውን ያዛል፤ (ይፈቅዳል)
የማህበሩን ዓመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርት፣ የሂሳብ መግለጫ፣ የኦዲት ሪፖርትና ዓመታዊ በጀት ያፀድቃል፣
ዓመታዊ የስራ ፕሮግራምን መርምሮ እቅድና በጀት ያፀድቃል፣
በጠንካራ ግልፅነትና ተጠያቂነት የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ስራውን ማከናወን እንዲችል የተለያዩ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፤
የቦርዱን የስብሰባ ሥነ-ስርዓት ደንብ ያወጣል፣
የማህበሩን የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድና በጀት ላይ በመምከር ያጸድቃል፣
የሚሰጡ ውሣኔዎችንና የሚወጡ እቅዶችን በሥራ አስኪያጁ ተግባራዊ መደረጋቸውን ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል፣
በስራ አስካያጅ ኮሚቴው የሚቀርቡትን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቶችን መርምሮ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል
የማህበሩን ፖሊሲ ለማውጣት ወይም ለማሻሻል የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ የሚያቀርባቸውን ሀሳቦች መርምሮ አስፈላጊም ሲሆን ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርባል።
የማህበሩን መፍረስና ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር መዋሃድ እንዲሁም ያለውን ንብረት ማጣራት በተመለከተ መርምሮ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፤
አንቀጽ 19፡ የቦርድ አባላት የስራ ዘመን
አጠቃላይ የቦርድ አባላት የስራ ዘመን ሦስት (3) ዓመት እና ሁለት(2) ዓመት ይሆናል። ፕሬዝደንቱ እና ፀሐፊው የስራ ዘመን ሦስት(3) ዓመት ይሆናል። ሌሎች የቦርድ አባላቶች የስራ ዘመን ሁለት(2) አመት ይሆናል ። የቦርዱ አመራርና ስራ እንዳይደናቀፍ ከጠቅላላው የቦርድ አባላት ቢያንስ የተወሰኑት በተከታዩ ዙር እንዲመረጡ ይደረጋል። ይህም ድጋሚ በተከታዩ ዙር የሚመረጡት ሰዎች ብዛት ከጠቅላላው የቦርዱ አባላት ቁጥር ታይቶ እንደሚከተለው ይወሰናል። የቦርድ አባላት ቁጥር ሁልጊዜ ሆን ተብሎ ጎዶሎ ቁጥር ስለሚሆን እንደ አባላቱ ብዛት እንደሚከተለው ተቀምጦአል። ድጋሚ የሚመረጡት ከ3 አባላት 1 ፤ ከአምስት አባላት 2፤ ከሰባት አባላት 3፣ ከ 9 ወይም ከ 11 አባላት ደግሞ 4 ቱ ተመልሰው በመመረጥ ለተጨማሪ ዓመት ያገለግላሉ።
በንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ የቦርድ አባላት የስራ ዘመን በሚያበቃበት ወቅት በአንቀፅ 34 ውስጥ በተጠቀሱት የቦርድ ምልመላና አተካክ ስርአት መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል።
አንቀጽ 20፡ መወገድ እና መልቀቂያ
የቦርድ አባላት እንዲሁም የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት ስራቸውን በአግባብ ካላከናወኑ ወይም የመስራት ብቃት ከጎደላቸው በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በተገቢ ሂደት ከስራቸው ይሰናበታሉ።
20.1 ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብቁ ባልሆነ የቦርድ አባላት ላይ ተገቢ ሂደት ያካሄዳል።
20.2 የስራ አስኪያጅ ኮሚቴው ብቁ ባልሆነ የኮሚተው አባል ላይ በሰብሳቢው የበላይ ተመልካችነት የቃል እና የፁህፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃ ይወስዳል። ከስራ አስኪያጅ ኮሚቴው አቅም በላይ ሲሆን ወደ ቦርዱ ያስተላልፋል።
20.3 የቦርድ አባላት ወይም የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባል በገዛ ፈቃዱ ማህበሩን መልቀቅ ከፈለገ ቢያንስ ከ 2 ወራት በፊት ለማህበሩ ማሳወቅና በወቅቱ በእጁ ላይ ያለ ማንኛውንም ዓይነት የማህበሩን ንብረት ማስረከብ፤ እየሰራ ያለው ትኩረት የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ወይም ስራ ካለ ቢቻል አጠናቅቆ ካልሆነም በቅንነት ለሚወከለው ሰው አስተላልፎ ይለቃል።
አንቀጽ 21፡ የቦርድ አመራር አካላት ስልጣንና ተግባራት
ቦርዱ ፤ ሰብሳቢውንና ምክትል ሰብሳቢውን ይመርጣል፣
የቦርድ አባል የሆነ ማናቸውም ሰው በተጨማሪ ኦዲተር ወይም ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሊሰራ አይችልም፣
የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ፀሐፊ ስልጣንና ተግባራቸውም የሚከተለው ነው፥
21.1. የቦርዱ ሰብሳቢ
የቦርዱን ስብሰባዎች ይጠራል ከጸሀፊው ጋር በመሆን አጀንዳዎችን ያዘጋጃል፣
የጉባዔውን ስብሰባ በሊቀመንበርነት ይመራል፣
ቦርዱ የሚያወጣችውን ደንቦችና የሚሰጣቸውን ውሣኔዎች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣
ቦርዱ ያጸደቃቸውን የሩብ ፣የግማሽ እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት እና እቅድ እንዲሁም አመታዊ የኦዲት ሪፖርቶችና የሂሳብ መግለጫ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት እና እንደ አስፈላጊነቱ ለተጠቃሚዎችና ለለጋሾች እንዲደርሱ ያደርጋል፣
ለቦርዱ የሚቀርቡ ጉዳዮችን ቅደም ተከተል በማውጣት ለውይይት እንዲቀርቡ ለፀሐፊው በአጀንዳነት ያስይዛል፣
ቦርዱ የሚያሳልፋቸው ውሣኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለሥራ አስኪያጁ መመሪያ ያስተላልፋል፣
የጸሃፊውን የሥራ አፈፃፀም በቅርብ ይከታተላል።
21.2. ምክትል ሰብሳቢ
ሰበሳቢው በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ ይሠራል፣
በሰብሳቢው ወይም በቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ሰራዎች ያከናውናል፣
21.3. ፀሐፊ
ከሰብሳቢው ጋር በመሆን ለጉባኤው አጀንዳዎችን ያዘጋጃል፣
የጉባኤውን ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይይዛል፣
የቦርዱን መዛግብትና ሠነዶች ይጠብቃል፣
በቦርዱ ሰብሳቢ ፊርማ የተላለፉ የቦርድ ውሳኔዎችን ይፈፅማል ያስፈፅማል።
21. 4. የሕዝብ ግንኙነት
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሁሉንም የፕሬስ መግለጫዎች ሙሉ በሙሉ ያስተባብራል; በAAB የቦርድ ኃላፊዎች እና በመገናኛ ብዙሃን መካከል ቃለ መጠይቅ ያዘጋጃል። የህዝብ ግንኙነት ሁሉንም የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ጨምሮ በህትመት፣ በኢንተርኔት፣ በሬዲዮ፣ በቲቪ እና በሌሎች ሚዲያዎች በኩል ማስተዋወቂያዎችን ያስተዳድራል።
21.5. የውስጥ ኦዲተር
የሂሳብ ክፍያ፣ ቼኮች፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ ወዘተ ጨምሮ ሁሉንም የፋይናንሺያል መረጃዎች የመመርመር ሃላፊነት ያለው ኦዲተሩ ነው።ኦዲተሩ ይከታተላል እና በጀቱን ያዘጋጃል። ኦዲተሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኦዲት ሪፖርቶችን ለዲሬክተሮች ቦርድ ያቀርባል ኦፕሬሽንን ለማሻሻል እና ለድርጅቱ የተሻለ የፋይናንስ አቋምን ያቀርባል።
አንቀጽ 22፡ የቦርድ ስብሰባ
የቦርዱ መደበኛ ስብሰባ በየሁለት ወሩ የሚካሄድ ሆኖ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያስፈልግ ግን በማንኛውም ጊዜ ልዩ ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፣
የቦርዱ አስቸኳይ ስብሰባ በማናቸውም ጊዜ በቦርዱ ሰብሳቢ ወይም ከቦርድ አባላ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሚጠይቁበት ጊዜ ሊካሄድ ይችላል፣
የቦርድ አባላት በስልክ ወይም በሌሎች ኢንተርኔት ላይ መሰረት ባደረጉ ስብሰባ የማካኼጃ መንገዶች ሊሳተፉ ይችላሉ፤ በአካል እንደተገኙም ይቆጠራል፣
ለቦርዱ መደበኛ ስብሰባ 15 የስራ ቀናት ለአስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ 5 የስራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ አባላት የስብሰባው ዝርዝር ጉዳይ፣ ቦታውንና ቀኑን እንዲያውቁት ይደረጋል፣
የቦርዱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፣
የቦርድ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች እንደየሁኔታው በአጀንዳነት ተይዘው ለውይይት ይቀርባሉ፣ ማንኛውም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲያዝለት የሚፈልግ አባል ቦርዱ ከመሰብሰቡ ቢያንስ ከአንድ ሳምንት በፊት ለቦርዱ ሰብሳቢ/ምክትል ሰብሳቢ/ ወይም ፀሐፊ በጽሁፍ ይህንኑ ማስታወቅ ይኖርበታል።
አንቀጽ 23: የቦርድ ድምጽ አሰጣጥ
ማንኛውም የቦርድ አባል ድምፅ በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ ያለው ድምፅ አንድ ብቻ ሲሆን ሁሉም አባላት እኩል ድምጽ አላቸው።
በቦርዱ የውሳኔ ሂደት ላይ በኢሜይል፣ በጽሁፍ፣ወይም ሌሎች አግባብ ባላቸው የሶሻል ሚዲያ ድህረ ገጾች ላይ በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት ይቻላል።
የድምጽ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ፍትሀዊ ነፃና ግልጽ በሆነ መንገድ ተፈፃሚ ይሆናል።
በድምፅ አሰጣጥ ወቅት የቦርድ አባላት ድምፅ በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ እኩል በኩል ከተከፈሉ የሊቀመንበሩ ሐሳብ ወሳኝ ይሆናል።
ከቦርዱ የተለየ ሃሣብ ያለው የማህበሩ አባል የልዩነት ሀሣቡን በቃለ ጉባኤው ላይ ለይቶ ማስፈር ይችላል።
የማህበሩ አብዛኛው ውሳኔዎች በ2/3 ድምጽ ይሻሻሉ ውይም ይፀድቁሉ።
አንቀጽ 24፡ የሥራ አስኪያጅ ተግባርና ኃላፊነት
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነቱ ለቦርድ ሆኖ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባሮች ይኖሩታል፥
ቦርዱ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት፤
የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ከ 5-11 አባላት ይኖሩታል፣
ማህበሩን ዋና መስሪያ ቤት የመለወጥና ቅርንጫፎች የመክፈት የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል፣
ማህበሩ ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር ህብረት ለመፍጠር አብሮ ለመስራት እቅድ አውጥቶ ለቦርድ ለውሳኔ ያቀርባል።
በማናቸውም አካል ዘንድ ማህበሩን ይወክላል፣ የማህበሩን ሥራ በተመለከተ ማናቸውንም ጉዳዮች ይፈጽማል፣ ውክልና ይሰጣል፣ በማህበሩ ስም የደብዳቤ ልውውጦችን ያደርጋል ውል ይዋዋላል፣
በማህበሩ ስም የባንክ ሂሳብ ይከፍታል፣ የሚከፈተውን የባንክ ሂሣብ እና ቼክ ወይም ሐዋላ ከሂሣብ ሹሙ ጋር በጣምራ ፊርማ ያንቀሳቅሳል፣
በቦርድ የሚተላለፉ ውሣኔዎችን ተግባራዊ ያደርጋል፣
በቦርዱ የፀደቀውን የሴክሬታሪያቱን ዓመታዊ በጀት በበላይነት ይመራል፣ወጪ ሆኖ በስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣በአግባቡ በስራ ላይ መዋሉንም ይቆጣጠራል፣
የሴክሬታሪያቱን የየሶስት ወር እና ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴና የፋይናንስ ሪፖርቶች እያዘጋጀ (በየሶስት ወሩ እና በየዓመቱ) ለቦርዱ ያቀርባል፣
የማህበሩን ፖሊሲ በማውጣትና የበጀት እና የሥራ እቅድ በማዘጋጀት ለቦርዱ ያቀርባል፣
በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የማህበሩ ሂሳብ እንዲመረመር ኦዲተር ይመርጣል፣ ያሰናብታል፣ክፍያውን ይወስናል፣
ፕሮጄክቶችን ለመተግበር በአጋር ድርጅቶች የቀረቡ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን በማጥናትና በመገምገም ለቦርዱ እና ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል።
በገንዘብ ወይም በማቴሪያል ለድርጅቱ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚሆኑ ገቢዎች መኖራቸውን ያረጋግጣል፣ ድጋፍ የሚገኝበትንም መንገድ ይቀይሳል፣
አንቀጽ 25፡ የስራ አስካያጅ ኮሚቴ የስራ ዘመን
አጠቃላይ የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት የስራ ዘመን (2) ሁለት ዓመት ይሆናል። የሥራ አስኪያጅ አባላት ቁጥር ሁልጊዜ ሆን ተብሎ ጎዶሎ ቁጥር ስለሚሆን እንደ አባላቱ ብዛት እንደሚከተለው ተቀምጦአል። ድጋሚ የሚመረጡት ዓባላት ቁጥር ብዛት በጠቅላላ ካሉት የኮሚቴ ዓባላት ጋር ሲነጻጸር በሚከተለው አሃዝ መሰረት ይሆናል። ከአምስት አባላት 2ቱ ፤ ከሰባት አባላት 3ቱ ፣ ከ 9 ወይም ከ 11 አባላት 4ቱ፤ ከ 13 ወይም ከ 15 ዓባላት ደግሞ 5ቱ ድጋሚ ተመርጠው ቀጣዩን ዙር ያገላግላሉ።
በንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት የስራ ዘመን በሚያበቃበት ወቅት በአንቀፅ 34 ውስጥ በተጠቀሱት የቦርድና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ምልመላና አተካክ ስርአት መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል።
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ስብሰባዎች ይጠራል ከጸሀፊው ጋር በመሆን አጀንዳዎችን ያዘጋጃል፣
25.1 ዋና ሰብሳቢ (ሊቀመንበር)
የጉባዔውን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት ይመራል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ የሚያወጣችውን ደንቦችና የሚሰጣቸውን ውሣኔዎች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ያጸደቃቸውን የሩብ ፣የግማሽ እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት እና እቅድ እንዲሁም አመታዊ የኦዲት ሪፖርቶችና የሂሳብ መግለጫ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት እና እንደ አስፈላጊነቱ ለተጠቃሚዎችና ለለጋሾች እንዲደርሱ ያደርጋል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ የሚቀርቡ ጉዳዮችን ቅደም ተከተል በማውጣት ለውይይት እንዲቀርቡ ለፀሐፊው በአጀንዳነት ያስይዛል፣
የሚያሳልፋቸው ውሣኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የስራ አስካያጅ ኮሚቴ መመሪያ ያስተላልፋል፣
የጠቅላላ የስራ አስካያጅ ኮሚቴዎችን የስራ ተግባሮችን እና አፈፃፀምን በቅርብ ይከታተላል።
25.2 ምክትል ሰብሳቢ (ም/ሊቀመንበር)
ሰበሳቢው በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ ይሠራል፣
በሰብሳቢው ወይም በቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ሰራዎች ያከናውናል፣
25.3 ፀሐፊ
ፀሐፊው ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
ከሰብሳቢው ጋር በመሆን ለጉባኤው አጀንዳዎችን ያዘጋጃል፣
የጉባኤውን ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይይዛል፣
የኮሚቴውን መዛግብትና ሠነዶች ይጠብቃል፣
በቦርዱ ሰብሳቢ ፊርማ የተላለፉ የቦርድ ውሳኔዎችን ይፈፅማል ያስፈፅማል።
ለዳይሬክተሮች ቦርድ የአስተዳደር፣ የቴክኒክና የማኔጅመንት እገዛ መስጠት፣
ለማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን፣ ፕሮጄክት ለማቅረብና ሪፖርት ለመፃፍ የሚረዱ ቅጾችን፣ደንቦችን፣ ወዘተ ማዘጋጀትና ቦርዱ እንዲያፀድቀው ማድረግ፣
የአጋር ድርጅቶችን ፕሮጄክት የማዘጋጀትና የመተግበር አቅም በመገምገም አስፈላጊውን እገዛ መስጠት፣
የቀረቡ ፕሮጄክቶችን ገምግሞ የማህበሩን ፈንድ መስፍርት ያሟሉትን ለቦርድ ውሳኔ ማቅረብ፣
ፕሮጄክቶችን የሚተገብሩ አጋር ድርጅቶችን የሚረዳ ለፕሮጄክት ዝግጅት፣ ለትገበራ፣ ለግምገማ እና ሪፖርት ለማድረግ የሚረዳ መምሪያ ፅሑፍ ማዘጋጀት፣
ፕሮጄክቶችን ከሚተገብሩ አጋር ድርጅቶች የሚቀርቡትን ሪፖርቶች ማቀናጀትና የማህበሩን አጠቃላይ የሩብ ዓመትና አመታዊ ሪፖርት ለቦርድ ማቅረብ፣
አንቀጽ 26: የሂሣብ ሓላፊ ተግባርና ኃላፊነት
ሂሣብ ሐላፊ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
ለሴክሬታሪያቱ እለት-ተለት ወጪ በስራ አስኪያጅና በሂሳብ ሐላፊው ፊርማ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሂሳብ እንዲከፈት ያደርጋል፤ እንቅስቃሴውንም ይከታተላል ይቆጣጠራል።
የማህበሩን ገቢና ወጪ ሂሣብ ይቆጣጠራል፣ በትክክል እንዲመዘገብና እንዲያዝ ያደርጋል፣
የማህበሩን ሂሣብ የሚንቀሳቀሰው በታወቀ የሂሣብ አሠራር ደንብ መሠረት መሆኑን ያረጋግጣል ይቆጣጠራል፣
የማህበሩን የባንክ ሂሣብና ቼክ ወይም ሐዋላ ከሥራ አስኪያጁ ጋር በጣምራ ፊርማ ያንቀሳቅሳል፣
እንደያስፈላጊነቱ የማህበሩን የሂሳብ አያያዝና ቁጥጥር በተመለከተ ረቂቅ ፖሊሲና መመሪያ አዘጋጅቶ በቦርድ ያፀድቃል፣
የማህበሩ የሂሣብ መዛግብት እና የተለያዩ ሰነዶች በጥንቃቄ እንዲያዙ ያደርጋል፣
የማህበሩን ሂሳብ አያያዝ፣ የአስተዳደር ቅልጥፍናና፣ቁጥጥር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማስቻል አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል በስሩ ያሉ ሰራተኞችን በአግባቡ ይመራል ያስተዳድራል፣
የሂሣብ መዝገብ፣ ገቢ እና ወጪ፣ ሀብት እና ዕዳን ያካተተ ሰነድ ያዘጋጃል፣
ለማህበሩ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ በሚሠማራበት ጊዜ ለዚሁ ሥራ የሚውሉ የተለያዩ የሂሣብ መዛግብት እንዲዘጋጁ ያደርጋል።
አንቀጽ 27፡ ገንዘብ ያዥ
ሂሣብ ሐላፊ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤ ቦርዱ ፤ የአማራ ማህበር በቤኤርያ ትሬዠር ሆኖ የሚያገለግለውን የገንዘብ ተቋም ወይም ባንክ የሚወስን ሲሆን ገንዘብ ያዡ የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል፥
ለአማራ ማህበር በቤኤርያ የሚተላለፈውን ገንዘብ በቦርዱ መመሪያ መሠረት በሓላፊነት ያስተዳድራል፣
ግለሰቦች እና ድርጅቶች ለአማራ ማህበር በቤኤርያ የሚያደርጉትን መዋጮና የገንዘብ ድጋፍ ተቀብሎ ወደ ማህበሩ ባንክ ሒሳብ ማስቀመጪያ ገቢ ያደርጋል፣
በባንክ የሚገኘውን የአ.ማ.ቤ ገንዘብ ቦርዱ በሚያወጣው የገንዘብ አያያዝና አስተዳደር ደንብ መሰረት ቀልጣፋና ጊዜን በማያባክን መንገድ ያስተዳድራል፣ የገንዘብ አጠቃቀምንም በተመለከተ የአማራ ማህበር በቤኤርያ የተለያዩ ዶኩመንቶች፣ መረጃዎችና ረፖርቶችን ያዘጋጃል፣
ፕሮጄክቶቻቸው በቦርድ ለጸደቀላቸው ተግባሪ ድርጅቶች የአማራ ማህበር በቤኤርያ የቦርድ ሊቀመንበር እና በዋና ሥራ አስኪያጁ በተፈረመ ደብዳቤ መሠረት የተፈቀደላቸውን ገንዘብ ያስተላልፋል፣
የተሰበሰበውን ገንዘብ አጠቃቀም በተመለከተ የሩብ ዓመትና ዓመታዊ ሪፖርቶችን አዘጋጅቶና ወቅቱን ጠብቆ ለሴክሬታሪያቱ ያቀርባል፣ በማህበሩ ድረ-ገፅ አማካኝነት ለደጋፊዎችና ለአባላት ግልፅ ይደረጋል።
ለሴክሬታሪያቱ እለት-ተለት ወጪ በስራ አስኪያጅና በሂሳብ ሐላፊው ፊርማ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሂሳብ እንዲከፈት ያደርጋል፤ እንቅስቃሴውንም ይከታተላል ይቆጣጠራል።
የማህበሩን ገቢና ወጪ ሂሣብ ይቆጣጠራል፣ በትክክል እንዲመዘገብና እንዲያዝ ያደርጋል፣
የማህበሩን ሂሣብ የሚንቀሳቀሰው በታወቀ የሂሣብ አሠራር ደንብ መሠረት መሆኑን ያረጋግጣል ይቆጣጠራል፣
የማህበሩን የባንክ ሂሣብና ቼክ ወይም ሐዋላ ከሥራ አስኪያጁ ጋር በጣምራ ፊርማ ያንቀሳቅሳል፣
እንደያስፈላጊነቱ የማህበሩን የሂሳብ አያያዝና ቁጥጥር በተመለከተ ረቂቅ ፖሊሲና መመሪያ አዘጋጅቶ በቦርድ ያፀድቃል፣
የማህበሩ የሂሣብ መዛግብት እና የተለያዩ ሰነዶች በጥንቃቄ እንዲያዙ ያደርጋል፣
የማህበሩን ሂሳብ አያያዝ፣ የአስተዳደር ቅልጥፍናና፣ቁጥጥር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማስቻል አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል በስሩ ያሉ ሰራተኞችን በአግባቡ ይመራል ያስተዳድራል፣
የሂሣብ መዝገብ፣ ገቢ እና ወጪ፣ ሀብት እና ዕዳን ያካተተ ሰነድ ያዘጋጃል፣
ለማህበሩ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ በሚሠማራበት ጊዜ ለዚሁ ሥራ የሚውሉ የተለያዩ የሂሣብ መዛግብት እንዲዘጋጁ ያደርጋል።
የማህበሩ የአመት የገንዘብ እሪፖርት በየዓመቱ January ላይ ይቀርባል። (January - December)
አንቀጽ 28፡ የሶሻል ሚዲያ እና የኢቬንት ዳይሬክተር
የሶሻል ሚዲያ እና የኢፌንት ዳሬክተር ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
የማህበሩን የቲውተር፤ የፎስቡክ፤ የኢንስተግራም እና የሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የቤኤርያን የአማራ ማህበርን ስራዎች እና ውይይቶች ያሰራጫል።
ከተለያዩ የቤኤርያን የሚወክሉ በፌዴራል በስቴት እና በስቲ ያሉን የአሜሪካ መንግስት መሪዎችን ግንኙነት ፈጥሮ፤ የማህበሩን ስራዎች እና አላም ያስተዋውቃል።
ከህዝብ ግኑኙነት እና የአድፎከሲ ዳይዴክተር እና ከሌሎች አመራሮች በመሆን የማህበሩን አላማ እና የማህበሩን የተለያዩ ስራዎች ያስተዋውቃል።
አንቀጽ 29፡ የአድፎከሲ እና የኮሚኒቴ ኢንጌጅመንት ዳይሬክተር
የአድፎከሲ ዳይሬክተር እና የኮሚኒቴ ኢንጌጅመንት አላፊ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
የማህበሩን አዳዲስ አባላት ይመዘግባል ይቆጣጠራል፤
ከተለያዩ የቤኤርያን የሚወክሉ በፌዴራል በስቴት እና በስቲ ያሉን የአሜሪካ መንግስት መሪዎችን ግንኙነት ፈጥሮ፤ የማህበሩን ስራዎች እና አላም ያስተዋውቃል።
ከተለያዩ የቤኤርያ የኮሚኒቲ አባላት ጋራ በመወያየት፤ የአማራ ማህበር በቤኤርያ ድጋፍ እንዲያገኝ ይሰራል።
በተለያዩ የማህበሩ ስብሰባዎች እና ውይይቶች ላይ የቤኤርያን የሚወክሉ የመንግስት አላፊዎችን እንዲገኙ ደብዳቤዎችን ይፁፋል፤ ይደውላል።
ከህዝብ ግኑኙነት እና ከሶሻል ሚዲያ ዳሬክተር እና ከሌሎች አመራሮች በመጣመር የማህበሩን አላማ እና የማህበሩን የተለያዩ ስራዎች ያስተዋውቃል።
አንቀጽ 30፡ ም/ የአድፎከሲ ዳይሬክተር እና የኮሚኒቴ ኢንጌጅመንት አላፊ
የአድፎከሲ ዳይሬክተር እና የኮሚኒቴ ኢንጌጅመንት አላፊ በማይኖርበት ግዜ ተክቶ ይሠራል፣ እንዲሁም ከዋናው የአድፎከሲ ዳይሬክተር ጋራ በመሆን ተባብሮ ይሰራል።
በኮሚቴው ወይም በቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ሰራዎች ያከናውናል፣
አንቀጽ 31፡ የህዝብ ግኑኝነት
የህዝብ ግኑኝነት አላፊ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
ማህበሩ ከተለያዩ የአማራ ማህበራት ጋራ እንዲወያይ፤ እንዲተዋወቅ ያደርጋል።
የማህበሩን አላማ እና ግቡ ለግለሰቦች ለድርጅቶች እና የአማራን ትግል ለሚደግፉ ሁሉ ገለፃ ያደርጋል።
31.1፡ ም/ የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ
ም/ የህዝብ ግኑኝነት አላፊ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል።
የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ በማይኖርበት ግዜ ተክቶ ይሠራል፣ ከህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ ጋር በመሆን ተባብሮ ይሰራል።
በኮሚቴው ወይም በቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ሰራዎች ያከናውናል፣
አንቀጽ 32፡ የጥናት፣ የትምህርት፤ እንዲሁም የምርመራ ጥናት ኮሚቴ ሀላፊ
የጥናት እና የምርምር የስራ ሒደት ሀላፊነቱ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
የማህበሩን ህልውና ይጠብቃል።
ለማህበሩ ኮሚቴ ወይም የቦርድ አባላት ሆነው የሚሾሙን ግለሰቦች ከቦርዱ እና ከኮሚቴው ጋር በመተባባር ድጋፍ እና ትብብር ያደርጋል።
በኢትዮጱያ ላይ ለአማራ ማህበረሰብ የሚደረጉ ድጋፎችን ከቦርዱ እና ከኮሚቴው ጋር በመተባባር ያማክራል።
የተቋሙን የፕሮጀክት ጥናት ያዘጋጃል ለኮሚቴው፤ ለቦርድ እና ለህዝቡ ያቀርባል።
የተቋሙን የደህንነት ስራ ይከተተላል። ከቦርዶች ለሚጠቆሙ ሰዎች ምልመላው ላይ ግለ ታሪክ እያየ ብቁነታቸውን ያማክራል።
የተፈናቃይ የአማራ ቤተሰብ ያጡትን የሚታገዙበትን ሁናቴ ለኮሚቴው ያቀርባል።
የፓለቲካ እና የታሪክ የትርክት አጀንዳዎችን በጥናት ያቀርባል።ያወያያል።
አንቀጽ 33: የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ስብሰባ
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ በየወሩ ወይም በየሁለት ወሩ የሚካሄድ ሆኖ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያስፈልግ ግን በማንኛውም ጊዜ ልዩ ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በማናቸውም ጊዜ በሰብሳቢ ወይም የስራ አስፈጻሚው አባላት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሚጠይቁበት ጊዜ ሊካሄድ ይችላል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴአባላት በስልክ ወይም በሌሎች ኢንተርኔት ላይ መሰረት ባደረጉ ስብሰባ የማካኼጃ መንገዶች ሊሳተፉ ይችላሉ፤ በአካል እንደተገኙም ይቆጠራል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ 15 የስራ ቀናት ለአስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ 5 የስራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ አባላት የስብሰባው ዝርዝር ጉዳይ፣ ቦታውንና ቀኑን እንዲያውቁት ይደረጋል፣
የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፣
የስራ አስፈጻሚ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች እንደየሁኔታው በአጀንዳነት ተይዘው ለውይይት ይቀርባሉ፣ ማንኛውም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲያዝለት የሚፈልግ አባል የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ከመሰብሰቡ ቢያንስ ከአንድ ሳምንት በፊት ለስራ አስፈጻሚው ሰብሳቢ/ምክትል ሰብሳቢ/ ወይም ፀሐፊ በጽሁፍ ይህንኑ ማስታወቅ ይኖርበታል።
አንቀጽ 34: የቦርድ ምልመላና አተካክ ሥነ-ሥርዓት
የአማራ ማህበር በቤኤርያ በሚያቋቁመው የቦርድ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት ጋር በመመካከር በተቀመጡ መመዘኛዎች መሰረት አዳዲስና ተተኪ የቦርድ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ የአባላትን በእጩነት ለጠቅላላ ጉባኤ ለውሳኔ ያቀርባል፣
የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የቦርድ አባላት ወይም የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት በድጋሚ እንዲያገለግሉ ከተፈለገ በጥቆማ ለአስመራጭ ኮሚቴ ለውድድር ቀርበው በድምጽ ብልጫ ይመረጣሉ፣
የማህበሩ የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት በማናቸውም ጊዜ ቢሆን የዲሞክራሲ መርሆችን የተከተለ ይሆናል፣
የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት እራሳቸውን ለቦርድ ምርጫ በዕጩነት ማቅረብ አይችሉም።
ቦርዱ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ በስራ ላይ ያሉ የቦርድ አባላት የስራ ዘመን ከማብቃቱ ከ90 የስራ ቀናት በፊት ተተኪ የቦርድ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላት ጥቆማ እንዲካሔድ ያደርጋል፣
ቦርዱ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አዲሶቹ ተመራጮች የነባር የቦርድ አባላት እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ የስራ ዘመን ባለቀ በ60 ቀናት ውስጥ ስራቸውን ተረክበው ይሰራሉ።
የቀድሞ ተመራጮች ከቦርድ አባልነት እንዲሁም በስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባልነት ከተሰናበቱም ዕለት ጀምሮ ከርክክብ በስተቀር ስራውን ማንቀሳቀስ አይችሉም፣
በጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳ ላይ ቀርበው ያልጸደቁና ያልሰፈሩ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጡ ውሣኔዎች ተፈፃሚነት አይኖራቸውም።
አንቀጽ 35፡ አጋር ማህበራት
የአማራ ማህበር በቤኤርያ ፤ ከአማራ ማህበረሰብና ለጋሽ ድርጅቶች የሚያገኘውን ገንዘብ ውጤታማ ለማድረግና ማንኛውንም ብክነት ለማስወገድ ስራውን የሚያከናውነው ከአማራ ማህበረሰብ ጋር ትስስር ያላቸውና በአካባቢው የልማት እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ተግባሪ ወይም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ነው፣
የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴና ፕሮጄክቶችን በመተግበር ጥሩ ልምድና የአሰራር ብቃት ማሳየት የቻሉ ህጋዊ እውቅና ያላቸው ተቋማት የሲቪል የልማት ድርጅቶች፣ የትምህርት የጤናና የመሳሰሉት የተራዶ ድርጅት ማህበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለአማራ ማህበር በቤኤርያ ተግባሪ አጋር ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ፣
ፕሮጄክት አቅራቢ፤ ተግባሪ አጋር ድርጅቶች ወይም እርዳታ ጠያቂ የሚመረጡት በሚያቀርቡት የፕሮጄክት ጥራትና ውጤት ተኮር መሆን፣ ከማህበሩ ዓላማ ጋር ያለው ጠንካራ ተያያዥነት፣ የመተግበር አቅምና የፕሮጄክቶችን እንቅስቃሴ ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር፣ ለመገምገምና ሪፖርት ለማድረግ ያለውን ችሎታ ወይም ብቃት አጥንቶ ቦርዱ በሚያጸድቀው መሠረት ይሆናል፣
አንቀጽ 36፡ የገንዘብ አጠቃቀም
ከአማራው ማህበረሰብ እና ከለጋሽ ድርጅቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለአማራ ማህበረሰብ ለሚጠቅሙ ወይም የአማራውን ህብረተሰብ አቅም ለሚያጠናክሩ ስራዎች በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቀርቦ በቦርድ ለፀደቁ ፕሮጄክቶች ማስፈጸሚያ ብቻ ይውላል፣
የአስተዳደር ወጪ ለመሸፈንና ሴክሬታሪያቱ በብቃት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ለሚያስፈልጉ እንደ ቢሮ፣ የቢሮ እቃዎች፣ መኪና እና የመረጃና የመገናኛ መሳሪያዎች የሚሆን በጀት ከአባላት መዋጮ ወይም ከሌሎች ለጋሽ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለማግኘት ጥረት ይደረጋል፣
አንቀጽ 37፡ ሕገ- ወጥ የገንዘብ ዝውውር ድርጊትን መከላከል
ወደ ማህበሩ የባንክ አካውንት የሚገባውን ገንዘብም ሆነ ፕሮጄክቶችን ለመተግበር የሚወጣው ገንዘብ ለሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም የሽብር ድርጊትን ለማገዝ እንዳይውል የሚመለከታቸው የድርጅቱ አስተዳደር አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄና ቁጥጥር ያደርጋሉ፣
ፕሮጄክት ተግባሪ አጋር ድርጅቶች በአሰራራቸውም ሆነ ከሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች ባላቸው ግንኙነት ለሙስና፣ ለሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ለሽብር ድርጊት ያልተጋለጡ መሆናቸውን ጸሃፊው የፕሮጄክት ሰራተኞችና የዳይሬክተሮች ቦርድ ገንዘብ ከመተላለፉ በፊት በቅድሚያ ያረጋግጣሉ።
አንቀጽ 38፡ ግልፅነትና ተጠያቂነት
ቦርዱ በሚያወጣው የፕሮጄክት ስምምነት ሰነድ አማካኝነት ከማንኛውም ፕሮጄክት ተግባሪ ድርጅት ጋር ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የፕሮጄክት ስምምነት ያደርጋል፣
የቦርድ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ በየሩብ (Quarter) አመቱ ጊዜያዊ የሂሳብ መግለጫ ያወጣሉ።
የቦርድ እና የስራ አስካያጅ ኮሚቴ አባላቱ ዓመታዊ የተረጋገጠ የሂሳብ መግለጫ ያወጣሉ። ዝርዝር የገቢ እና የወጪ ምንጭንና አጠቃቀሙን ጨምሮ ያቀርባል፤ የቀረበውም ሪፖርት በድርጅቱ ድረ-ገፅ ለአባላት ይፋ ይደረጋል፣
ፕሮጄክት ተግባሪ አጋር ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ሪፖርት በማጠናከርና በማጠቃለል ጸሃፊው የሩብ ዓመትና ዓመታዊ ዝርዝር ሪፖርት ከነበጀት አጠቃቀሙ በማዘጋጀት በድረ-ገፁ አማካኝነት ወቅቱን ጠብቆ ለአባላት ይፋ ያደርጋል፣
የማህበሩ ቦርድ፣ እንዲሁም የስራ አስካያጅ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ የድርጅቱን ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢ የሆኑ የአሰራር ሂደቶችንና መመሪያዎችን ያወጣሉ ተግባራዊነታቸውንም ያረጋግጣሉ፣
ማንኛውም የማህበሩ እንቅስቃሴ በድረ-ገፁ አማካኝነት ለአባላት ይፋ እንዲሆን ይደረጋል፣
በማህበሩ ድረ-ገፅ የሚተላለፉት መረጃዎች የመዋጮውን አካሄድ፣ የቦርድ ውሳኔዎችን፣ በግምገማ ላይ ያሉ ፕሮጄክቶችና የፀደቁ ፕሮጀክቶች ብዛትና ዓይነት፣ ፕሮጄክቶቹ ያሉበት ሁኔታ… ወዘተ የሚያካትት ይሆናል።
አንቀጽ 39፡ የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ስለማሻሻል
ይሄ ደንብ የመጀመሪያ እትም እንደመሆኑ መጠን ከኮሚቴ ዓባላትም ሆነ በዓባልነት ተመዝግበው ካሉ ዓባላት የማሻሻያ ገንቢ ሃሳቦች ሊሰነዘሩ ይችላሉ። ይህ ዓይነት ሃሳብ ለማህበሩ መጠናከር አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ቦርዱ በዓመቱ አንዴ እነዚህን ሃሳቦችና አስተያይቶች ተመዝግበው ለጠቅላላ ጉባኤው እንዲቀርቡ በማድረግ ስብሰባው ላይ ከተገኙት አባላት ከ 2/3 በላይ ድምጽ የሚያገኙት ማሻሻያዎች ደንቡ ላይ ይጨመራሉ ወይም ይስተካከላሉ።
የመተዳደሪያ ደንቡ የሚሻሻለው የማሻሻያ ሀሳቡ 2/3ኛ በላይ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በተገኙበት የቦርድ ስብሰባ 2/3ኛ ድምጽ ሲያገኝ ነው።
አንቀጽ 40፡ የማህበሩ መዋሃድና መለወጥ
ማህበሩ ወደ ተለያዩ ድርጅቶች የሚከፋፈለው፣ ከሌላ ተመሳሳይ ድርጅት ጋር የሚዋሃደው ወይም ወደ ሌላ አይነት ድርጅትነት የሚለወጠው ከአምስት አባላት 3ቱ ፤ ከሰባት አባላት 5ቱ ፣ ከ 9 ወይም ከ 11 አባላት 7ቱ፤ ከ 13 ወይም ከ 15 ዓባላት ደግሞ 11ዱ በሆነ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ካለፈ በሃላ ወደ ቦርዱ ቀርቦ የቦርዱ ዓባላት ደግሞ ከአምስት አባላት 3ቱ ፤ ከሰባት አባላት 5ቱ ፣ ከ 9 ወይም ከ 11 አባላት 7ቱ፤ ከ 13 ወይም ከ 15 ዓባላት ደግሞ 11ዱ ተስማምተው ካፀደቁ በሁዋላ ለጠቅላላው ጉባዔ ቀርቦ በእለቱ ከተገኙት የጠቅላላ ጉባኤው ዓባላት በ2/3ኛው ድምፁ ሲያገኝ ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል።
ውህደቱን ወይም መከፋፈሉን በተመለከተ የሚደረገውን ድርድር የሚያከናውነው በጠቅላላ ጉባኤው፤ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ምክትል ሰብሳቢ እና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሚያካትት ይሆናል።
አንቀጽ 41፡ ስለማህበሩ መፍረስ
ማህበሩ የሚፈርሰው ጠቅላላ ጉባኤ ማህበሩ እንዲፈርስ በ2/3 ኛ ድምፅ ሲወስን ነው።
ማንኛውንም የማህበሩን ገንዘብና ንብረት ጨምሮ ተመሳሳይ አላማ ላላቸው የአማራ ድርጅቶች በማሰተላለፍ አፈጻፀሙን ለጠቅላላ ጉባዔውና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ያስታውቃል፤ ሪፖርትም ያደርጋል።
አንቀጽ 42፡ ይህ የመተዳደሪያ ደንብ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ የመተዳደሪያ ደንብ የመጀመሪያው እትም ተጠናቅቆ በመስራች አባላቱ ድምፅ ከጸደቀበት ከ July 24, 2023 ዓ/ም ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡ ይህ ደንብ የጠቅላላ ጉባዔውን ድምጽ ያካተተ ይሆን ዘንድ ከላይ እንደተጠቀስው በዓመት አንድ ጊዜ ከጠቅላላው ጉባዔ የሚቀርቡ ማሻሻያዎች ካሉ በመሰብሰብ ለጉባዔው ለውይይትና ለድምጽ በማቅረብ በእለቱ ከተገኙት የጉባዔው አባላት በ 2/3 ኛ ድምጽ የሚያልፉት ማሻሻያዎች ህጉ ላይ ይጨመራሉ።
ሕጉ በየዓመቱ የሚሻሻልበት ቀን የመጀመሪያው ደንብ በጸደቀበት ወር ይሆናል። ነገር ግን ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በዚያ ወር መካሄድ ካልቻለ ቦርዱ ተወያይቶ ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ሊያስተላልፈው ይችላል።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠር ባለ መልኩ የተዘጋጀው የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ህጋዊ የመተዳደሪያ ደንባችን ነው። በአማርኛ ቋንቋ በሰፊ የተተነተነው ይሄ የመተዳደሪያ ደንባችን ደግሞ ለውስጥ አሰራር እንድንጠቀምበት ተብሎ የተዘጋጀ ነው።በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተተረጓመው ይሄን ሙሉ ትንታኔ የያዘው የመተዳደሪያ ደንብ እንደአስፈላጊነቱ ለሚጠይቁ ሰዎች ሊታደል ይችላል።